መምህር ግርማ ወንድሙ በዋስ ተለቀቁ
በማታለል ወንጀል ተጠቅጥረው በእስረ ላይ የነበሩት መምህር ግርማ ወንድሙ ዛሬ በዋስ ተለቀቁ።
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከመርማሪ ፖሊስ የተጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሳይቀበል ነው የዋስትና መብታቸውን የጠበቀላቸው።
በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ወሰን አካባቢ የአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤትን እምነታቸውን በመጠቀም በ2006 እስከ ጥር 30 ይህን ቤት ለቀው ካልወጡ አስከሬንዎ ይወጣል በማለት በማስፈራራት ግለሰቡ እጅግ በጣም አነስትኛ በሆነ ዋጋ በ700 ሺህ ብር እንዲሸጡ እና ይህንንም ገንዘብ ልፀልይበት ብለው ወስደዋል በሚል በማታለል ወንጀል መጠርጠራቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ጥቅምት 18 ቀን 2008 ፖሊስ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ችሎቱ 7 ቀን ፈቅዶ እንደነበርም አይዘነጋም።
ከዚያ በኋላ በተጠርጣሪው ቤት በተደረገው ብርበራ ፖሊስ 8 የሞባይል ሲም ካርዶችን ማግኘቱንና የተጠርጣሪው ግብረ አበር እየተፈለገ መሆኑን በመጥቀስ እነዚህን ቀሪ የምርመራ ስራዎች አጠናቀሮ ለመቀጠል ተጨማሪ 14 ቀን ቢጠይቅም ፍርድ ቤቱ ከኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶቹ በማን ስም ወጡ እና የያዙትን መረጃ ለመጠባበቅ 5 ቀን ፈቅዶ ነበር ውጤቱን ለመስማት ለዛሬ ቀጠሮ የያዘው።
በዛሬው ችሎት መምህር ግርማ እስክነጠበቆቻቸው በችሎቱ ቀርበዋል።
መርማሪ ፖሊስ ከችሎቱ በተሰጠህ ጊዜ ምን ሰራህ? ምንስ ይቀርሃል? ተብሎ ሲጠየቅ፥ የሲም ካርዶቹ የያዙትን መረጃ ለማግኘት ደብዳቤ በትኛለሁ፤ ነገር ግን ከኢትዮ ቴሌኮም ቅርንጫፎች መረጃዎቹ ወደ ዋና ቋት ያልገቡ በመሆኑ ከዋናው መስሪያ ቤት ማጠቃለያ ይቀረኛል፤ እንዲሁም የተጠርጣሪው አንድ ግብረ አበር ለመያዝ እየተደረገ ያለው ክትትል በሂደት ላይ ሲል መልሷል።
በመሆኑም እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ የምርመራ ስራዎችን ለማስቀጠል እንዲያመቸው ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።
የተጠርጣሪው ጠበቃ በበኩላቸው ባለፈው ቀጠሮ ከኢትዮ ቴሌኮም የሚመጣውን ውጤት ለመጠባበቅ ብቻ በመሆኑ ፖሊስ በዛሬው ቀጠሮ በዚህ ረገድ ምንም የሰራው ስራ የለም ብሏል።
እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ተጠርጣሪ ለመያዝ በባለፈው ቀጠሮ ተጨማሪ ጊዜ አልፈቀደም የሚለውንም አክሏል።
አንድን ተጠርጣሪ አስሮ ሌላ ተጠርጣሪ ማፈላለግ ህጉ እንደማይፈቅድ እና ደንበኛችን የተጠረጠሩበት ወንጀልም የዋስትና መብት የሚከለክል ባለመሆኑ በተመጣጣኝ ዋስትና ደንበኛችን እንዲለቀቁ ሲል አመልክቷል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ የመርማሪ ፖሊስን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ 50 ሺህ ብር አስይዘው ከእስር ይለቀቁ ሲል ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በዚህ መሰረት መምህር ግርማ ወንድሙ በዚህ በተጠረጠሩበት የማታለል ወንጀል የተነፈጋቸው የዋስትና መብት ተከብሮላቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መምህር ግርማ ወንድሙ በሌላ በተጠረጠሩበት ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ለህዳር 3 2008 በተያዘው ቀጠሮ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ይሆናል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ