አቀጣጣዮቹ እነማን ናቸው?ዘመቻው ከሁሉም እውነተኛ ድጋፍ ይሻል
የኢትዮጵያ
ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት ባካሄዱት መራራ ትግል በእጃቸው ያስገቧቸውን ድሎች ማጣት በፍፁም አይፈልጉም።ባለፉት
አመታት በፖለቲካ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ያስመዘገቧቸውን እጅግ ጣፋጭ
የትግል ውጤቶችን በመንከባከብ ግስጋሴያቸው ወደ ፊት እንጂ ለአፍታም ቢሆን ወደ ኋላ እንዲመለስ የማይፈልጉ
መሆናቸውን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ባሳላፏቸው ታላላቅ ውሳኔዎች አረጋግጠዋል።
የሕዝቦች
ትግል ጉዞ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ እንደማይጓዝ የታወቀና የተረጋገጠ ጉዳይ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች
በቁርጥ ቀን ልጆቻቸው እልህ አስጨራሽ ትግል የተጎናፀፏቸውን ድሎች ለመንጠቅ የተለያዩ ኃይሎች በመፍጨርጨር ላይ ይገኛሉ።
ባለፈው
አመት በተካሄደው አምስተኛ አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ብስጭት ውስጥ ለመዘፈቅ የተገደዱት እነዚህ ፀረ ሰላም ኃይሎች የኢትዮጵያ
ልማትና እድገት ቀጣይ እንዳይሆን የሚችሉትን ነገር ሁሉ በማድረግ ላይ ናቸው።
ለዚህ
በማሳያነት ሊጠቀስ የሚችለው ለምነው በቃረሟቸው ዶላሮች በውጭ አገራት ባቋቋሟቸው ሚዲያዎች በማሰራጨት ላይ ያሉት የሃሰት
ፕሮፓጋንዳ ነው።በአገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እነርሱ እያሉ እንዳሉት አይደለምና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከምንም
እንደማይቆጥሯቸው ስለሚታወቅ የእነዚህስ እዳው ገብስ ነው ብሎ ማለፍ በቂ ነው።
አሁን
አሳሳቢው ጉዳይ በአገር ውስጥ ያለው ነውና እስኪ በአገራችን ጉዳዮች ላይ እንኪያ ስላንትያ አንባባል።
መቼም
የሰሞኑ የአገራችን ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግር ላይ አትኩሮ ለሶስት ወራት የተካሄደው ሳይንሳዊ ጥናት ይፋ መደረግ ጉዳይ
ነውና እዚህ ላይ በማትኮር የኢህአዴግ ቱባ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ ያለምንም መሸፋፈን ሲወያዩ ብዙዎች አይተዋል፤ሰምተዋል
የየራሳቸውን አስተያየትም እየሰጡ ነው።መወያየቱስ ሸጋ ነው ግልፀኝነቱ ያስደስታል ግን ችግሩስ ዘላቂ መፍትሄ ያገኝ ይሆን?
ብለው የጥርጣሬ አስተያየት የሚሰጡ ዜጎችም እንዳሉ ተስተውሏል።
እንግዲህ
መንግስት መልካም አስተዳደር ተረጋግጦ የሁሉም ዜጎች ተጠቃሚነት በተግባር እንዲታይ ቁርጠኛና የማያወላውል አቋም
እንዳለው አሳይቷል፤ፈረሱም ይኽው ሜዳውም ይኽው ሲል በይፋ
አውጇል።አሁን ከእነማን ምን ይጠበቃል?
የአገራችን ሚዲያዎች
የአገራችን
ሚዲያዎች የመልካም አስተዳደርና ሙስና ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ መስራት ይችላሉ።በአገራችን የሚገኙ የግሉም የመንግስትም
መገናኛ ብዙሃኖች በአንዳንድ አካላት ራሳቸው መገናኛ ብዙሃኑ በፈጠሯቸው ክፍተቶች ምክንያት አዝማሪ ናቸው የሚል ያልተገባ ስም
የተሰጣቸው ቢሆኑም በአንፃራዊነት ሲታይ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ሰርተው ሕዝቦችን ማነቃነቅ የሚያስችል አቅም ገንብተዋል።
በዚህ
አቅም ተጠቅመው የአገሪቱንም ሕጎች በማክበር በመረጃ ላይ የተመሰረቱ ትክክለኛ ዘገባዎችን ለአንባቢና አድማጭ ተመልካቾች
በማቅረብና በማጋለጥ የፀረ ሙስና ትግሉን ማፋፋም
ይጠበቅባቸዋል።ይህን ምቹ አጋጣሚ መጠቀም ለራስም ለአገርም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያስገኛልና ይታሰብበት።
ኪራይ
ሰብሳቢው ኃይል የበላይነት ካገኘ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሕልውናም ጥያቄ ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው።ስለዚህ ሁሉም
የአገራችን መገናኛ ብዙሃኖች የአወቁሽ ናቅኩሽ አካሄድን ትተው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙና ኪራይ
ሰብሳቢው ኃይል አንገቱን ደፍቶ በመጨረሻም ቅስሙ ተሰብሮ እንዲጠፋ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል።
የአገራችን ብሄር
ብሄረሰቦችና ሕዝቦች
የኢትዮጵያ
ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት ተካባበረውና ተዋደው አብረው ኖረዋል።ይህ አኩሪና ተደናቂ የሆነ አብሮነታቸው አሁንም
ቀጥሏል።የአብሮነቱ ጉዞ እንዳይቀጥልና በተለያዩ ምከንያቶች ተደናቅፎ ከመንገድ እንዲቀር በጠባብነት በትምክህተኝነትና
በአክራሪነት የተጀቦኑ ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎች እንዳሉ ግልፅ ነው።
በመንግስት
መዋቅሮች ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኘው ኪራይ ሰብሳቢ ኃይል
አይኑን አፍጥጦ የመጣበትን ጠላት ለመከላከል ቢፍጨረጨርም ከቁርጠኛ የመንግስት አካላትና ከሕዝቦች የበለጠ አቅም የለውምና የትም
መድረስ አይችልም።እዚህ ላይ ከሕዝብ የተደበቀ ምንም ነገር የለም የሚለውን እውነታ መያዝ ያስፈለጋል።
የፀረ
ሙስናና መልካም አስተዳደር ችግሮች ዘመቻ ከግቡ ሊደርስ የሚችለው ሁሉም ያለምንም ማቅማማትና ስጋት መታገል ሲችል ብቻ ነው።
ሙሰኛው
ማነው? ከህዝብ የተሰጠውን አደራና ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ለግል ጥቅሙ ብቻ እየተራሯጠ ያለ ማነው? ልማታዊ ካልሆኑ
ባለሃብቶች ጋር የእጅና ጓንት አይነት ግንኙነት ያለው ማነው?ሕዝቦችን በአግባቡ ባለማገልገል የመልካም አስተዳደር ችግር የተስፋ
አስቆራጭነት ደረጃ ላይ እንዲደርስ እያደረገ ያለ ማነው? ጉበኛው ማነው? በኔት ወርክ የሚንቀሳቀሰው ማነው?አስመሳዮችስ እነማን
ናቸው?የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ በሕዝቦች ዘንድ ይገኛል።ለጥያቄዎቹ ትክክለኛውን ምላሽ በመስጠት ለፀረ ሙስናና መልካም
አስተዳደር ችግር መፍትሄ ዘመቻ የሕዝቦች ድጋፍ አስፈላጊው ነው።
የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና
ኮሚሽን
ኮሚሽኑ
ከምስረታው ጊዜ ጀምሮ የማይናቁ በርካታ ስራዎችን አከናውኗል።ከሕዝብና መንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለግል ጥቅምና
ብልፅግና ባዋሉ ግለሰቦች ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ
አድርጓል፤ሌሎች ያልተደረሰባቸው ሌቦች የልብ ትርታም እንዲጨምር በማድረግ የስጋት ኑሮ ላይ እንዲወድቁ ምቹ ሁኔታዎችን
ፈጥሯል።ነገር ግን በተሰጠው ትልቅ ስልጣንና ኃላፊነት ደረጃ ልክ ሰርቷል ወይ? ሲሉ የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው።
ከአመታት
በፊት ሕግ ወጥቶሎት የተጀመረው የባለስልጣናትና ተሿሚዎች ሃብትና ንብረት ምዝገባ ውጤት ለሕዝብ ለምን ይፋ አይደረግም?የሚል
ጥያቄም አሁን የብዙዎቸ ሆኗል።የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሃኖች በተለያዩ ወቅቶች የምዝገባው ውጤት
ለህዝብ ይፋ ሳይደረግ የቆየባቸውን ምክንያቶች ቢደረድሩም ይህ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም።
የባለስልጣናትና
ተሿሚዎች ሃብትና ንብረት ምዝገባ ውጤት ለሕዝብ ይፋ መደረግ የፀረ ሙስና ትግሉን ለማጠናከርና የሚፈለገውን ውጤት ለማስገኘት
ያስችላል፤ኮሚሽኑ ግን እስከ አሁን ድረስ ይህን ማድረግ አለመቻሉ ለትዝብት እንዲጋለጥ አድርጓል።ለመሆኑ ብዙዎች የስነ ምግባርና
ፀረ ሙስና ኮሚሽን እራሱ ከሙስና የፀዳ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳላቸው ኮሚሽኑ ያውቅ ይሆን?ክቡር ኮሚሽን ሆይ ለመልካም
አስተዳደር ችግሮች መፍትሄና ለብልሹ አሰራሮች መወገድ ያንተም አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለሆነ የወቅቱን ትኩሳት ተረድተህ አለሁ
በል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ