አስመሳይነትና አድርባይነት ይዘመትባቸው!



አስመሳይነትና አድርባይነት የመርህ አልባነት መገለጫ ናቸው፡፡ በራሳቸው የማይተማመኑና በፅናት የሚቆሙለት ዓላማ የሌላቸው ሰዎች፣ በመርህ ከመመራት ይልቅ ለሕገወጥ ተግባራት ይጋለጣሉ፡፡


በአገሪቱ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለሙስና መስፋፋት አሉታዊ ሚና ከሚጫወቱ ሕገወጦች ባልተናነሰ፣ አስመሳዮችና አድርባዮች ቀላል የማይባል ሚና አላቸው፡፡ ሕገወጥ ተግባራትን አይቃወሙም፡፡ ብልሹ አሠራሮችን አይነቅፉም፡፡ ፍትሕ ሲዛባ ግድ የላቸውም፡፡ በአጠቃላይ ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ያስቀድማሉ፡፡ እንደግፈዋለን የሚሉትን ፓርቲና መንግሥት ሳይቀር ለጉዳት ይዳርጋሉ፡፡ የመውቀስ፣ የመተቸት፣ የመገሰፅና የማረም ተግባር ኃላፊነታቸው መሆኑን እያወቁ፣ የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት ሲሉ ብቻ ገደሉን ሜዳ ነው ይላሉ፡፡ በሐሰት መረጃ ያሳስታሉ፡፡  

በቅርቡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገር አቀፍ ደረጃ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ በተሠራ ጥናት ላይ ባደረጉት ውይይት፣ በተለያዩ መስኮች ውስጥ የታዩ አሳሳቢ ጉዳዮች ተወስተዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ገብተው የችግሮቹን ግዝፈትና አሳሳቢነት በጥናት ላይ ተመሥርተው ያቀረቡት የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ መንግሥት በተቻለ ፍጥነት ተገቢውን የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡ መንግሥት ለመፍትሔ የሚሆኑ ግብዓቶችን ማግኘት የሚችለው ግን፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ለለውጥ የሚተጉ ዜጎችና ጠንካራ የሕዝብ አገልጋዮች ከጎኑ ሲሠለፉ ነው፡፡

እንደ ሥጋት ከሚታዩ በርካታ ችግሮች መካከል አንዱ የሚዲያው ነፃነት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ‹‹ኔትወርክ›› እየተባለ በሚጠራው የሕገወጦች ስብስብ ምክንያት ዓላማው የሚደናቀፈው፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ (ፐብሊክ) ሚዲያዎች ውስጥ በመሸጉ ኃይሎች ነው፡፡ ሚዲያው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲወገድ፣ ዘረኝነትና ጠባብነት ቦታ እንዳይኖራቸው፣ የመንግሥት ጠንካራ ጎኖች እንደሚወደሱ ሁሉ ድክመቶችም እንዲተቹ፣ ወዘተ. ተግቶ እንዲሠራ ከማድረግ ይልቅ፣ ተዓማኒነት የሌለውና ልፍስፍስ እንዲሆን አድርገውታል፡፡ የሕዝብን አቤቱታና እሮሮ እያፈነ፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች እያድበሰበሰና የቡድንተኞች ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ ጠንከር ብለው ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚሞክሩ ሲኖሩ ደግሞ እየተኮረኮሙ ሞራላቸው ይላሽቃል፡፡ በዚህ ምክንያት የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ እየጠፋ የመንግሥት ሚዲያ እንጨት እንጨት እያለ ነው፡፡ የአስመሳይነትና የአድርባይነት ውጤት ይኼ ነው፡፡ 

በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ የሚያደርጋቸው፣ በአስመሳዮችና በአድርባዮች በመከበባቸው ነው፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አንድን ተቋም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማስተዋወቅና ዝናውን የማስተጋባት ትልቅ ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ ብዙዎቹ ተቋማት ለዚህ ወግና ማዕረግ አልበቁም፡፡ ተቋማቱ ምርቶቻቸውን ወይም አገልግሎቶቻቸውን በሚገባ አሻሽለው ለሚዲያ ወይም ለሕዝብ እንዲተዋወቁ ማገዝ ሲገባ፣ ከሕዝብ የተደበቁና ግልጽነት የጎደላቸው ሆነዋል፡፡ በአስመሳይና በአድርባይ የሕዝብ ግንኙነት ሰዎች አማካይነት አቅም የሌላቸው አመራሮች ራሳቸውን እየደበቁ፣ የብዙኃን ሠራተኞችን ልፋት ገደል ይከቱታል፡፡ ለሚዲያ መረጃ ለመስጠት ብርድ ብርድ የሚላቸው፣ ዘገባዎችን ለማስተባበል ግን የሚቀድማቸው የለም፡፡ ያውም ሀቅ ሳይኖራቸው፡፡ ፖስት ካርድ፣ ካሌንደርና ብሮሸር እያሳተሙ ‹‹መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ›› በማስባል ያስተርታሉ፡፡ ተቋማቱና አመራሮቹ እንዲጠናከሩ ከማድረግ ይልቅ መደባበቅ በጣም በዝቷል፡፡ አስመሳይነትና አድርባይነት በዚህም ይገለጻል፡፡ 

ተቋማት በዕውቀትና በክህሎት እየተመሩ በሕግ የተሰጡዋቸውን ኃላፊነቶች መወጣት ሳይችሉ ሲቀሩ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ይንሰራፋባቸዋል፡፡ በኔትወርክ የተሳሰሩ ሙሰኞች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ከብቃት ይልቅ ትውውቅና የጥቅም ግንኙነት ይነግሣል፡፡ በቅጥር፣ በምደባ፣ በሹመት፣ በዝውውር፣ በትምህርት ዕድልና በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች አድሎአዊነት ይንሰራፋል፡፡ በሕግ የተሰጠ ሥልጣን ያላግባብ የጥቅም ማጋበሻ ይሆናል፡፡ የአገልጋይነትን መንፈስ በማዳፈን ሥርዓት አልበኝነት እንዲንሠራፋ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ለእንዲህ ዓይነቱ መራር ችግር መፍትሔ ለመፈለግ በቁርጠኝነት የሚነሳ ከሆነ፣ ከአስመሳይነትና ከአድርባይነት የፀዱ ወገኖችን ነው ከጎኑ ማሠለፍ ያለበት፡፡ በኔትወርክ የተቧደኑት የጥፋት ይዞታቸውን ላለማስነጠቅ በሚያደርጉት ትንቅንቅ፣ ጠንክሮ የሚፋለማቸው በራሱ የሚተማመን ኩሩ ዜጋ እንጂ አስመሳይና አድርባይ አይደለም፡፡ 

በአገሪቱ በጣም አሰልቺ ከመሆኑ የተነሳ የዜጎች መንገፍገፍ የታየበት ሌላው ትልቁ ችግር ስብሰባ መሆኑ ተወስቷል፡፡ ስብሰባ ዋነኛው የአስመሳዮችና የአድርባዮች መደበቂያ ነው፡፡ ከሥራ ይልቅ ለወሬ ቅርብ የሆኑት እነዚህ ኃይሎች በስብሰባ ወቅት በተግባር የማይተረጎሙ ንድፈ ሐሳቦችን በመተንተን፣ የማይፈልጓቸውን ወገኖች በማመናጨቅና በማስፈራራት፣ የሕዝብ ቅሬታዎችን በማዳፈንና ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማይዛመዱ ጉዳዮችን በማመንዥክ በአገርና በሕዝብ ጊዜና ሀብት ላይ ይቀልዳሉ፡፡ መልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን፣ ሙስና እንዳይጠፋና ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ እንዳይሆን እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ ከጥቅም ተጋሪዎቻቸው ህልውና ጋር የተቆራኘ መፈክር በማስተጋባት አስመሳይነትንና አድርባይነትን ያስፋፋሉ፡፡ 

ብዙዎቹ በአደባባይ የመንግሥት ወይም የገዥው ፓርቲ ታማኝ ጠበቃ አድርገው በማቅረብና የባለሥልጣናትን ስም በመጠቀም፣ ያልተገባ ጥቅም በማጋበስ የሌሎችን መብት ይዳፈራሉ፡፡ ዝናና ክብር ያዋርዳሉ፡፡ እነዚህ የተሳሰሩ ኃይሎች ብዙኃኑን ሰጥ ለጥ በማድረግ እንደፈለጋቸው ይጨፍራሉ፡፡ እነዚህና አይዞህ ባይ የበላዮቻቸው የመንግሥት ሚዲያና ተቋማትን ባያልፈሰፍሱ ኖሮ፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የመንግሥትና የሕዝብ ነው የተባለው መሬት የደላላ መጫወቻ ይሆን ነበር? በሥልጣናቸው ያላግባብ የሚገለገሉ ግለሰቦች የሞራልና የሥነ ምግባር ደረጃ እንዲህ ይዘቅጥ ነበር? ሕዝብ የሙሰኞች ሰለባ ይሆን ነበር? የሕዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ይዳፈኑ ነበር? በጥቅማ ጥቅምና በብሔር ግንኙነት የተደራጁ ኃይሎች እንዲህ ይፈነጩ ነበር? ለመሆኑ መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ የሚተማመኑባቸው አባላትና ደጋፊዎች የሚሳተፉባቸው ማኅበራትና አደረጃጀቶች የት ነው ያሉት? የጠራ ምላሽ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሮች ሲከሰቱና አደጋ ሲፈጥሩ ዝም ብለው ከማየት ይልቅ፣ የማረምና የመገሰጽ ኃላፊነት ስላለባቸው ነው፡፡ በተግባር ግን የሉም፡፡  

አስመሳይነትና አድርባይነት ከመጠን በላይ እየሰፋ በመጣ ቁጥር የግልጽነትና የተጠያቂነትን መርህ ያጠፋል፡፡ አምባገነንነት ይንሠራፋል፡፡ በየቦታው ትንንሽ ‹‹ንጉሦች›› ይፈጠራሉ፡፡ ጠባብነትና ዘረኝነት ያቆጠቁጣል፡፡ ሕገወጥነት ይሰፍናል፡፡ እንኳን ስለ ዴሞክራሲና ስለ ሰብዓዊ መብት መነጋገር ይቅርና ወጥቶ መግባት በራሱ ይቸግራል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ይደፈርሳል፡፡ መንግሥት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ የሚያሳስቡትን ዋነኛ ጉዳዮች ከልብ ለመቅረፍ ከተነሳ፣ በመጀመሪያ በአስመሳይነትና በአድርባይነት የተተበተበውን የገዛ ራሱን ሚዲያ ነፃ ያውጣ፡፡ ሚዲያውን እያልፈሰፈሱ የፍርኃት ቆፈን የለቀቁበትን ያፅዳ፡፡ ጠንካራ ሚዲያ በሌለበት የመልካም አስተዳደር አስከፊ ችግሮች አስተካክላለሁ ማለት በፍፁም የማይሞከር ነው፡፡

በሌላ በኩል አስመሳይነትና አድርባይነት በውስጡ የሰፈነ መንግሥት ከመርህ ይልቅ ገጠመኝ ይበዛዋል፡፡ መርህ አልባነት ደግሞ ከመንግሥት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ አስመሳይነትና አድርባይነት የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት፣ የራስ ወዳድነት፣ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነት፣ የዓላማ ቢስነት፣ የፈሪነትና የሕገወጥነት መገለጫ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ለአገርም ሆነ ለሕዝብ የማይጠቅምና ታሪክ የሚያጎድፍ ድርጊት አሽቀንጥሮ መጣል ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው አስመሳይነትና አድርባይነት ይዘመትባቸው የሚባለው!  

ምንጭ:ሪፖርተር

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa