በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ስር ሳይሰዱ ሊፈቱ ይገባል

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ኢትዮጵያ የጀመረችው የሰላምና የልማት ጉዞ እንዳይደናቀፍ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ስር ሳይሰዱ ሊፈቱ ይገባል አለ።


የጉባዔው የበላይ ጠባቂዎችና የስራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት ምሽት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት እንደተገለፀው በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ከማህበራዊ ግንኙነት በተጨማሪ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው ስር ሳይሰዱ ሊፈቱ ይገባል።

በቅርቡ ሁከትና ብጥብጥ በተከሰተባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች በተከሰተ የሰላም መደፍረስ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ መሰረተ ልማት፣ ንብረትና የኃይማኖት ተቋማትን የማውደም ተግባርም ተፈፅሟል።

በመሆኑም ችግሮቹ ስር ሳይሰዱ እንዲፈቱና በአገሪቱ የተጀመረው ልማት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን እንደሚያስተምሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገልጸውላቸዋል።

የኃይማኖት መሪዎች በሰላም ግንባታና ህዝብን በማረጋጋት ስራዎች ላይ ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውኑ ከመንግስት አካላት በቂ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም የበላይ ጠባቂዎቹ ጠይቀዋል።

መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እያስመዘበ መሆኑን የገለፁት የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎች በየደረጃው ያሉ አመራሮች በቀላሉ ሊመለሱ የሚችሉትን የህብረተሰቡ ጥያቄዎች በአፋጣኝ መፍታትና የህብረተሰቡን እርካታ መጨመር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እንዲኖርና የኃይማኖትም ሆነ የመንግስት ተቋማት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የኃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተማር ላይ መሆናቸውን የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።

ወጣቶች የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ የሚፈልጉትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ የአገራቸውን ሰላም ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የኃይማኖት አባቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ ጠንካራ ተግባር እያከናወነ መሆኑንና ይህንኑ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን ተናግረዋል።

መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት በቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኃይማኖት አባቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም የማስተማር ስራውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ወጣቶችን በማስተማር እንዲለወጡ እየተደረገ መሆኑንና የብጥብጥና የጥፋት መሳሪያ ሊያደርጓቸው በሚፈልጉ አካላት እንዳይታለሉ ማስተማርና መምክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አገራዊና ኃይማኖታዊ ተልዕኮውን ለመፈፀም በሰላም እሴት ግንባታ ላይ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman