በኦሮሚያ ምዕራብ አርሲ ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት ሰባት ፖሊሶች ተገደሉ

ቁጥራቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች ተገድለዋል
የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ተቃጥለዋል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት ሰባት የፖሊስ አባላት ተገደሉ፡፡ በፖሊስ አባላትና በታጣቂዎቹ መካከል በተፈጠረው በዚህ ግጭት ግን የሞቱት የታጣቂዎች ቁጥር አልተገለጸም፡፡


ግጭቱ የተቀሰቀሰው ሰኞ የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከተገደሉት ሰባት የፖሊስ አባላት በተጨማሪ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት፣ ማሳዎች፣ ደንና የመንግሥት ተቋማት መቃጠላቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ የተቀሰቀሰበት ምክንያት እየተጣራ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የታጠቁት ሰዎች መስጊድና ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር ማቃጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ አርሲ ዞን የተቀሰቀሰው ግጭት በተለይ ሻላ፣ ሲራሮና ሻሸመኔ ወረዳዎች ውስጥ በስፋት ተከስቶ ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የግጭቱ መንስዔ የፖለቲካ ይዘት ያለው ዘፈን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በኦሮሚያ ክልል እንዳይዘፈን የተከለከለው የአጫሉ ሁንዴ ዘፈን በአንድ ሠርግ ላይ ይዘፈናል፡፡ ዘፈኑን ለምን አዘፈናችሁ የሚል ጥያቄ ካቀረቡት የፖሊስ አባላት ጋር በተፈጠረው አለመግባባት፣ ግጭቱ መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በምዕራብ አርሲ ዞን በተቀሰቀሰው ግጭት ሰባት የፖሊስ አባላት፣ ቁጥራቸው ያልታወቀ ታጣቂዎች እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ወደ 12 የሚደርሱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

አሁን የተቀሰቀሰው ግጭት በቅርቡ በኦሮሚያ ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር የሚያያዝ መሆኑን የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፣ የግጭት ባህሪ የተቀየረና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ሳይቀር ያነጣጠረ በመሆኑ ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን የግጭቱ መንስዔ እየተጣራ በመሆኑ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም ግጭቱ የተከሰተበት የምዕራብ አርሲ ዞን በአሁኑ ወቅት መረጋጋቱን ገልጸው፣ የአካባቢው ሽማግሌዎችም ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባሩ እንዲመለስ የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች ግን በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መከሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ተግባራዊ መደረግ የለበትም በሚል በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ከ140 በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከሦስት ሺሕ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የገለጹት የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች የተደበደቡ፣ የቆሰሉና የደረሱበት ያልታወቀ ሰዎች መኖራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ግጭት ሞት፣ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪ በሕዝብ መገልገያዎች፣ በግለሰቦች ንብረት፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በተሽከርካሪዎችና በመሳሰሉ ንብረቶች ላይ እስካሁን መጠኑ ያልታወቀ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ከሕዝብ በደረሰበት ጫና የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን እንዲቆም የወሰነ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ክልል የሚገኘውን የማስተር ፕላኑን ክፍል ብቻ ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡


ምንጭ ሪፖርተር

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa