የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2009 በጀት አመት ከ274 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አስተላለፈ

የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2009 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት  ከ274 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ።


የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2009 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፏል።

የምክር ቤቱ ጽሀፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የ2009 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት 274,373,197,248 (ሁለት መቶ ሰባ አራት ቢሊዮን ሶስት መቶ ሰባ ሶስት ሚሊዮን አንድ መቶ ዘጠና ሰባት ሺህ ሁለት መቶ አርባ ስምንት ብር) እንዲሆን ወስኗል።

ለ2009 በጀት ዓመት በፌዴራል መንግስት ለሚከናወኑ ስራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን በጀት አጽድቆ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወቅት ስራ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን መግለጫው አስታውሷል።

በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወሰነው ቀመር መሰረት የፌዴራሉ መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የድጋፍ በጀት መጠን መወሰን እንዳለበት መግለጫው አመልክቷል።

ስለዚህም ከሃምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም በሚፈጸመው በአንድ በጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተመደበው በጀት በ2007 ዓ.ም ከጸደቀው ጋር ሲነጻጸር የ13 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አሳይቷል።

ከፌዴራል በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 68,792,874,848 ብር፣  ለካፒታል ወጪ 105,708,615,000 ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 87,871,707,400 ብር እና ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 12,000,000,000 ብር  እንዲሆን ተመድቧል።

የ2009 እስከ 2013 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ ፊዚካል ማእቀፍ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለበጀት ዝግጅት መነሻ በማእቀፍነት እንዲያገለግል መደረጉንም አመልክቷል።

በማእቀፉ ላይ በመመስረትም የ2009 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት በጀት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ስራዎች ላይ በማተኮር በዝርዝር ተዘጋጅቷል።

በጀቱ በአግባቡ ለተመደበለት አላማ ህግና ስርአትን ተከትሎ በቁጠባ ስራ ላይ እንዲውልና የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል የገቢ አሰባሰብ ስርአት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ለተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ አስተላልፎታል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርጅትን ማቋቋሚያ ደንብን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።

አየር መንገዱ ያለበትን ጠንካራ የገቢ ውድድር በማሸነፍ በአትራፊነት ለመቀጠል ያስችለው ዘንድ የካፒታል መጠኑ ወደ 60 ቢሊዮን ብር ከፍ ተደርጎ በመንግስት እንዲፈቀድ የቀረበውን ማሻሻያ ምክር ቤቱ ተቀብሎታል።

በተጨማሪም  ኢትዮጵያ ከ11 አገሮች ጋር ባደረገቻቸው የትብብር ስምምነቶች ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በመቀበል ለማጽደቅ ለህዝብ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

Source:ENA



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa