"አንድነት አንድ ዓይነትነት" አይደለም!
"እኔ በኢትዮጵያዊነት ነው የማምነው" እያሉ ፉን ፉን የሚሉ ሰዎችን በዓይነ ሕሊናዬ እየታዘብኩ ነው
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሃሳባቸውን የሚገልፁ ሰዎች የዘር ፌዴራሊዝም አሁኑኑ መፍረስ አለበት እያሉ ሲያላዝኑ የሚውሉ ናቸው፤ይህን አቋማቸውን ሲገልፁ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩና እየኖሩ ያሉ አይመስሉም
ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ ለብሔር ጉዳይ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶ ኢትዮጵያዊነት ተዘነጋ፤ይህ ትክክል አይደለም መታረም አለበት በሚል እምነት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እየተሰራ ነው
ኢትዮጵያዊነት ይጠናከራል ግን ደግሞ ብሔራዊ ማንነት ሊተው የሚችል አይደለም እኩል መራመድ ይችላሉ ሲባሉ ንጭንጭ ሲያደርጋቸው እየተመለከትን ነው፤"አንድነት አንድ ዓይነትነት" አይደለም ተብሎ የተነገራቸውም የተዋጠላቸው አይመስሉም
በነገራችን ላይ ከዚም ከዚያም ኢትዮጵያዊነት እያሉ ሲጮሁ የሚውሉ ሰዎች ለኢትዮጵያ ምንም ነገር ያልሰሩ በተግባር ለኢትዮጵያ ያልቆሙ ስሟን ብቻ በመጥራት ሲያንቆለጳጵሱ የሚውሉ በችግሯ ጊዜ ያልደረሱላት ናቸው፤ይህ እውነት ሲነገራቸው ደስ አይላቸውም
ኢትዮጵያዊነት እያሉ ሲዘፍኑ ቢውሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መቀየር አይችሉም!ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታላቅ አገር ናት ይህን እንዴት መካድ ይቻላል?ለማንኛውም ጭቅጭቁ፤ንዝንዙ በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥረት መሰረት ለውይይት ቀርቦ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበት ይመስለኛል
ይህን ጉዳይ እንዳስታውስ ያስገደደኝ 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ነው
ቀኑ እንዳለፉት ዓመታት በአንድ መድረክ በመገናኘት የፓናል ውይይት በማካሄድና በባሕላዊ ዘፈኖች በመጨፈር ብቻ የሚታለፍ እንዳልሆነ እየተነገረ ነው የልማት ስራዎች ምልከታ ይኖራል የበጎ ስራ አገልግሎትም የሚሰጥበት ነው መልካም ነው! ተወደደም ተጠላም ይህም የለውጡ ውጤት ነው
ቀኑ በክልሎች በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፤እንደ አገር ማጠቃለያው በውቧ ሃዋሳ ከተማ ሕዳር 29, 2015 ዓ.ም ይሆናል
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ