"ኢትዮጵያ ያገኘችው የዲፕሎማሲ ውጤት በሀገሪቱ መንግሥትና ሕዝብ ጥንካሬ የተገኘ ነው"
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ኢንስቲትዩት ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አንዳንድ ምዕራባውያን ለኢትዮጵያ በነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ በሀገሪቱ የራሳቸውን አሻንጉሊት መንግሥት ለማስቀመጥ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡
ሆኖም በሕዝብና መንግሥት በአንድነት በሠሩት ሥራ የምዕራባውያኑ ሴራ ሊከሽፍ ችሏል፡፡ ከምንም በላይ ምዕራባውያን በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በሌሎች ሰበቦች ተጠቅመው እጃቸውን ለማስገባት ይጠቀሙበት የነበረው የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጦርነት ኢትዮጵያ በፈለገችው መልክና ልክ ተጠናቋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ካገኘችው ሰላም በተጨማሪ የዲፕሎማሲ ድሎችን እንድትቀዳጅ ዕድል የከፈተ አንዱ ምክንያት ሲሆን የተገኘው የታየው የዲፕሎማሲ እምርታም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት አንድነትና ጥንካሬ የተገኘ ነው ብለዋል፡፡
አሁን ያለው የዲፕሎማሲ ድል ኢትዮጵያ ታግላ በበላይነት ያመጣችው ድል ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ፤ የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያን ለመጣል ያልፈነቀለው ድንጋይ እንዳልነበር ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በጋራ፣ በትብብርና በአንድነት የተቃጣባቸውን የጠላት ኃይል ጥቃት በመመከታቸው ምክንያት ድል አድርገዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በባሕሪያቸው ማንም ይሁን ማን በተቻለ አቅም የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከብርላቸው አካል እንደሚፈልጉ የተናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ፤ በዚህም ሀገራቱ ከጥቂት ወራት በፊት በሰብዓዊ መብት ስም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያደርጉ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ይህ ጫና አልፎ በአሜሪካና በአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ ተጋባዥ መሆን መቻሏን አንስተው፤ የኢትዮጵያ በዚህ ጉባዔ ላይ መጋበዝ ትልቅ እንድምታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጠላትነት ተፈርጆ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት በጉባዔው ላይ ተጠርቶ መሳተፉ በራሱ ትልቅ ድል ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ ገለጻ፤ ምዕራባውያን እንደፈለጉ የሚያዙት መንግሥት በኢትዮጵያ ለማስቀመጥ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያደረገውን ጦርነት በበላይነት በማሸነፉ ኢትዮጵያ የማትበገር አገር መሆኗን እንዲያረጋግጡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ይህም ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዕድገት አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡
በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት በዲፕሎማሲው ረገድ ጠንካራ ሥራ እየሠራ ስለነበር አሜሪካን ጨምሮ የሎች ሀገራትን ልብ ያሸነፈበት ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ከምታደረገው ዲፕሎማሲ አልፎ ተርፎ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አለመረጋጋት ስለሚታይበት ይህንን አለመረጋት ሊፈቱ ከሚችሉ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ኢትዮጵያ መሆኗን በማሰብ ጭምር የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እንዳጠናከሩ ገልጸዋል፡፡
ምንጭ: ኢፕድ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ