ዘላቂ የግጭት መቋጫ ስምምነቱ ይሳካ ይሆን?




በትግራይ ክልል ጦርነት የተጀመረበት ጊዜ ሁለት ዓመቱን ሊደፍን አንድ ቀን ሲቀረው፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ ከሳምንት በኋላ ኅዳር 3 ቀን ደግሞ በናይሮቢ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል ስምምነት የሁለቱ ወገኖች የጦር አመራሮች ስምምነት በኬንያ ናይሮቢ ተከናወነ፡፡
ሁለቱ ስምምነቶች ከተፈረሙ በኋላ በተጨባጭ በትግራይ ክልል ተስፋ ሰጪ ለውጥ መታየት ቢጀምርም፣ በስምምነቱ መሠረት ይፈጠራል ተብሎ የሚጠበቀው የተሟላ ለውጥ እየታየ አለመሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡
በአሥር ቀናት ውስጥ የሕወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንደሚፈቱ፣ እንዲሁም በአንድ ወር ጊዜ ክልሉን የመከላከያ ሠራዊት ሙሉ ለሙሉ ይቆጣጠራል ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ግን ሲሆን አልታየም፡፡ ታጣቂዎቹ በከፊል ትጥቅ መፍታታቸውና ከአንዳንድ ግንባሮች መልቀቃቸውን ይፋ ቢያደርጉም፣ የትጥቅ መፍታቱ ሒደት እክል እንደ ገጠመው ሲነገር ቆይቷል፡፡
ለሕወሓቶች ትጥቅ ያለ መፍታት ምክንያት ደግሞ የኤርትራ ጦርና ከመከላከያ ውጪ ያሉ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ለቀው አለመውጣታቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ በዚህ የትጥቅ መፍታት ሒደት አለመተግበር የተነሳም፣ በአጠቃላይ ጅምሩ የሰላም ሒደት ባለበት ተቸንክሮ መቆሙ ሲነገርም ነበር፡፡
ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በናይሮቢ የሁለቱ ወገኖች የጦር መሪዎች የተፈራረሙት ሦስተኛው ዙር ስምምነት ግን፣ ይህንን ክፍተት ይሞላል እየተባለ ነው፡፡ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም (Permanent Cessesions of Hostility) የተባለው ይህ ቀጣይ ዙር የሰላም ስምምነት፣ ስድስት አንቀጾችን በስምንት ገጽ ይዞ የቀረበ የስምምነት ሰነድ አለው፡፡
ይህ ሰነድ በዋናነት ሰላም በተጨባጭና በተግባር መተርጎም አለመተርጎሙን የመከታተል ሒደትን የያዘ ነው፡፡ አዲሱ ስምምነት ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ንግግር የሚቀጥልበትን መንገድም የሚጠርግ ነው እየተባለ ነው፡፡
አዲሱ ዙር ስምምነት የሰላም ስምምነቱን ትግበራ የሚከታተል ቡድን የሚዋቀርበትን ሁኔታ በግልጽ ያስቀመጠ ነው፡፡ የአፍሪካ የባለሙዎች ቡድን (Team of African Experts) ይቋቋማል በማለቱ፣ ይህኛውን ስምምነት ከቀደሙት ተመሳሳይ ስምምነቶች የተለየ ያደርገዋል እየተባለም ነው፡፡
ስምምነቱን ካፈራረሙትና ከአደራደሪዎቹ አንዱ የሆኑት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ‹‹በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት መቀሌ ተገኝተን የሰላም ስምምነቱን ትግበራ እንከታተላለን፡፡ አሁን የስምምነት ሰነድ ሳይሆን ተጨባጭ ዕርምጃ ነው የሚያስፈልገው፤›› በማለት መናገራቸው ድርድሩን የሚመሩት አካላት የሰላም ስምምነቱ በፍጥነት እንዲተገበር ያላቸውን ፍላጎት ማሳያ ነው እየተባለ ይገኛል፡፡
በአዲሱ ሰነድ መሠረት የስምምነቱን አተገባበር የሚከታተል፣ የሚያረጋግጥና ቅሬታ የሚሰማ አካል ቡድን ይዋቀራል፡፡ ‹‹ይህ ቡድን ደግሞ ያለ ገደብና በነፃነት እየተንቀሳቀሰ ሥራውን ይሠራል፤›› ነው ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ፡፡ በዚህ የባለሙያዎች ቡድን ውስጥ ደግሞ ሕወሓት፣ የፌዴራል መንግሥት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥትት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች ውክልና እንደሚኖራቸው ነው በስምምነቱ የተመለከተው፡፡
የባለሙያዎቹ ቡድን የሕወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ የሚፈቱበትን ሒደት ይከታተላል፣ ታጣቂዎቹ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማዕከላት የሚገቡበትን ሒደትና የመልሶ ማቋቋሙን ሥራ ይከታተላል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠርበትን በትግራይ ሰላምና ፀጥታ የማስከበሩን ኃላፊነት የሚረከብበትን ሒደትም ይከታተላል ተብሏል፡፡
ኡሁሩ ኬንያታ የስምምነቱን መፈረም ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፣ የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ይወጣሉ የሚል መረጃ ሰጥተው ነበር፡፡
ይህንን የበለጠ የሚያጠናክር መግለጫ ያወጣው የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት፣ የውጭ ግንኙነትና የደኅንነት ፖሊስ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ፣ ‹‹ኤርትራ ከትግራይ ክልል ትውጣ፤›› የሚል አቋም አንፀባርቋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት መግለጫ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ለሰላም ስምምነቱ መተግበር በጎ ሚና እንዲጫወቱ ይጠይቃል፡፡ ኤርትራን በስም በመጥቀስም እ.ኤ.አ. በ2000 ዓ.ም. በተፈረመው የአልጀርስ ስምምነት መሠረት፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2018 ይፋ በሆነው የኢትዮጵያ ኤርትራ ሰላም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ጦር ከትግራይ መሬት ለቆ እንዲወጣ መግለጫው ጥሪ ያቀርባል፡፡
ይህ ደግሞ የዋና አደራዳሪው የአፍሪካ ኅብረት መግለጫን ከማጠናከር በዘለለ፣ ‹‹የኤርትራ ጦር በትግራይ ክልል መቆየት ለሰላም ስምምነቱ ትግበራ እንቅፋት እየፈጠረ ነው፤›› የሚል መግባባት፣ የድርድሩን ሒደት በቅርበት በሚከታተሉ ወገኖች ዘንድ መፈጠሩን ማረጋገጫ ተደርጎ እየቀረበ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁንም ቢሆን፣ ‹‹የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ ክልል ገብቷል›› የሚለውን ጉዳይ በይፋ ማረጋገጫ ሲሰጥበት ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ለሰላም ስምምነቱ እንቅፋት በመሆናቸው፣ የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ይውጡ በመባሉ ምክንያት፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ የኤርትራ ኃይሎች እንዲወጡ ወደ መጠየቅ ሊገባ ይችላል፤›› የሚሉ ቢኖሩም፣ ‹‹ይህንን ማድረግ የኤርትራ ጦርን ወደ ትግራይ ክልል መግባት በይፋ አምኖ መቀበል ነው፤›› የሚሉም አሉ፡፡
‹‹የውጭ ኃይሎች ይውጡ›› የሚለው ጥሪም ሆነ ግፊት፣ አሁንም ቢሆን በጥቅሉ እንጂ በጠራ መንገድ አለመቀመጡን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡
የውጭ ኃይሎች የሚለው ከመከላከያ ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎችን የተመለከተ መሆን፣ አለመሆኑ አልተብራራም ይባላል፡፡ ከኤርትራ ኃይሎች እኩል ከትግራይ መውጣት አለባቸው የሚባሉት የአማራና የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎችን ጉዳዩ ይመለከታቸው እንደሆነ በስምምነት ሰነዶቹ ተብራርቶ አለመቀመጡን የሚያወሱም አሉ፡፡
የቀደሙት ሁለት ዙር ስምምነቶች ከተፈረሙ አንድ ወር አለፋቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሕወሓት ታጣቂዎች ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ፈተው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መላው ትግራይን መቆጣጠር እንደነበረበት በብዙዎች ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡
አሁን በትግራይ ክልል ብዙ የተለወጡ ነገሮች ቢኖሩም፣ ኅብረተሰቡ ከሰላም ስምምነቱ ማግሥት የጠበቀው በጣም ብዙ እንደነበር፣ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከሚሰጡት አስተያየት መታዘብ ይቻላል፡፡
በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት መጀመሩ፣ ተቆራርጦ የቆየውን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከቀሪው ኢትዮጵያ ክፍልና ከመላው ዓለም ጋር ያገናኘ ትልቅ ለውጥ እየተባለ ነው፡፡
ብዙ ቅሬታ ቢቀርብም የረድዔት አቅርቦቱ ከዚህ ቀደም በተሻለ ሁኔታና በተሻለ አማራጭ እየተካሄደ እንደሚገኝ ብዙ ማረጋገጫዎች አሉ፡፡ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የባንክ አገልግሎቶች መጀመራቸው፣ የሰላም ስምምነቱ ያስገኛቸው ትልልቅ ውጤቶች መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
ይህ ሁሉ በጎ ለውጥ በትግራይ ክልል ቢታይም፣ የሰላም ስምምነቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳና በተጠበቀው ሁኔታ ወደ መሬት ባለመውረዱ በክልሉ በርካታ ችግሮች እንደተፈጠሩ ሲነገር ቆይቷል፡፡
ለአብነት ያህል ባለፈው ሳምንት መንግሥትና ሕወሐትን ያካሰሰው፣ በመቀሌና በአንዳንድ የትግራይ ከተሞች አለ የተባለውን ዘረፋና ሕገወጥነት መጠቀስ ይቻላል፡፡
መንግሥት የተደራጁ የዘረፋ ወንጀሎች በመቀሌና በአንዳንድ አካባቢዎች መኖራቸውን፣ ታኅሳስ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ለዚህ ምክንያት ብሎ መንግሥት ያቀረበው ደግሞ የሕወሓት ኃይሎች በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ትጥቅ ባለመፍታታቸው፣ መላው ትግራይን መከላከያ መቆጣጠር ባለመቻሉ የፀጥታ ክፍተት መፈጠሩን ነበር፡፡
መንግሥት ይህንን ባለ በማግሥቱ ሕወሓት ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ የሰላም ስምምነቱ መተግበር እንቅፋት የመንግሥትና የኤርትራ ኃይሎች መሆናቸውን ሲከስ ታይቷል፡፡ ይህ የሁለቱ ወገኖች መካሰስ ደግሞ አካባቢውን መልሶ ወደ ግጭት የሚከት ነው የሚል ግምት ሲያሰጥ ነው የከረመው፡፡
ይህ አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ሦስተኛው ዙር ስምምነት በናይሮቢ በሁለቱ ወገኖች የጦር መሪዎች መፈረም መቻሉ፣ ‹ግጭቱ ሊመለስ ይችላል› የሚለውን ሥጋት ቢያንስ የሚያቀል እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የትግራይ ክልልን ሁኔታ የሚከታተሉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ሁለቱ ወገኖች መልሰው ወደ ግጭት ሊገቡ የሚችሉበት ምዕራፍ መዘጋቱን ነው የሚናገሩት፡፡ አሜሪካኖች በሰጡት ዋስትና የሰላም ስምምነቱ በጥቂቱ ወደ ትግበራ መግባቱን ያስታወሱት ተንታኙ፣ አሁንም ቢሆን የአሜሪካኖች ግፊት ከፍተኛ መሆኑን ያወሳሉ፡፡
ምዕራባውያኑ በዋናነት በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት መጠመዳቸውንና ይህ እየቀጠለ እንደሚሄድ ተንታኙ ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ ደግሞ ሌላ ጫና እንዳይፈጥርባቸው፣ እንዲሁም ለራሳቸው ዓለም አቀፍ ገጽታ ተዓማኒነት ሲሉ ከዳር እንዲደርስ ይፈልጋሉ ይላሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የሰላም ስምምነቱ ወደ መሬት መውረዱ የማይቀር መሆኑንና ጦርነት እንደገና እንደማያገረሽ ነው ግምታቸውን የሰጡት፡፡
በአዲሱ የግጭት በዘላቂነት የመቋጫ ስምምነት መሠረት ሁለቱ ወገኖች ከሰላም ስምምነቱ ትግበራ ጎን ለጎን ወደ ፖለቲካ ንግግሮች እንደሚገቡ ተመልክቷል፡፡ መንግሥትም ሆነ ሕወሓት ችግር ቢያጋጥም እንኳ ለሚቋቋመው ሒደቱን ተከታታይ የባለሙያዎች ቡድን ችግራቸውን አቅርበው በሰላም እንዲፈታ ጥረት ያደርጋሉ እንጂ፣ በፍፁም ጠመንጃ አያንሱም ተብሏል፡፡ አዲሱ ስምምነት እንደተጠበቀው ዘላቂ ሰላም የማስገኛ ምዕራፍ ይሆን ዘንድ የብዙዎች ምኞት ነው፡፡
ምንጭ: ሪፖርተር ጋዜጣ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman