የብልፅግና ፓርቲ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሄድ ነው

 


ብልጽግና ፓርቲ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን በመጪው አርብ ህዳር 30 በሀዋሳ ከተማ ሊያካሄድ ነው።ፓርቲው አስቸኳይ ስብሰባውን የጠራው፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰረት የፓርቲውን ኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትን በድጋሚ ለመምረጥ መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፓርቲው አንደኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው ከስምንት ወራት በፊት በመጋቢት 2014 ዓ.ም ነበር። ብልጽግና ፓርቲ በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው፤ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጦ ነበር።

አስራ አንድ አባላት ያሉበት የፓርቲው ኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላት ምርጫም የተከናወነው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነበር። የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት እና በብልጽግና ፓርቲ የቀረቡለትን ሰነዶች ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን አባላትን ምርጫ ውድቅ የሚያደርግ ውሳኔ ባለፈው ነሐሴ ወር አሳልፏል።

የኮሚሽኑ አባላት አመራረጥ ሂደት፤ በምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ እና በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ያልተከተለ መሆኑን ቦርዱ በውሳኔው ላይ አስፍሯል። በዚህም መሰረት ፓርቲው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት፣ በድጋሚ የኮሚሽኑን አባላት እንዲመርጥ፤ ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር።

ብልጽግና ፓርቲ የተሰጠው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ጊዜ ቢቀረውም፤ በመጪው አርብ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ መወሰኑን የፓርቲው ምንጮች ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፓርቲው አባላት፤ ለአንድ ቀን በሚካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ እንዲገኙ ጥሪ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa